የሐረር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ታሪክ

የሐረር ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ታሪክ ሐረር ከአዲስ አበባ በመቀጠል ከዛሬ 120 ዓመት በፊት ሶፊ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ሀጂ አብደላ ሙስሊህ (ሓጂ ቧንቧ) በተባሉ ግለሰብ አማካኝነት ሐረርን በዘመናዊ መንገድ በቧንቧ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ አድርገዋት ነበር፡፡

በመቀጠልም በ1920ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ከሶፊ ምንጭ በተጨማሪ የጀኔላ እና የንጉስ ሽራ ምንጮችን በማጎልበት የውሃ አቅርቦት እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ ቀስበቀስ የህዝብ ቁጥር ብዛቱ እየጨመረ የውሃ ፍላጎት አቅርቦቱ ጋር አልጣጣም በማለቱ ሌላ የውሃ መገኛ ሥፍራ ለማግኘት በ1953 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ከሐረር 18ኪ/ሜ ርቀት በመሄድ የሐረማያ ውሃ ተጣርቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል ተመረጠ፡፡ በዚህም መሠረት የሐረማያ ውሃ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታው ተከናውኖ በ1959 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ተመርቆ ለሐረር ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

የሐረማያ ሐይቅ ውሃ ቀደም ብለው አገልግሎት እየሰጠ ከነበሩት ምንጮች ጋር በመጣመር ግንባታው ሲጠናቀቅ ለቀጣይ 30 ዓመታት እስከ 70,000 ለሚደርስ ህዝብ የውሃ ፍላጎት መሸፈን እንዲችል ታስቦ ቢሰራም በጊዜ ሂደት የሐረማያ እና አወዳይ ከተማ እየተስፋፋ መምጣት እንዲሁም የሐረር ከተማ ህዝብ ብዛት እየጨመረ ከመምጣቱ በላይ በእርሻ ስራ የሚተዳደሩ በአጎራባች ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች የሐይቁን ውሃ እንደ መስኖ በመቁጠር በሞተር በመሳብ ለእርሻ ሥራ አገልግሎት እየተጠቀሙበት በሌላ በኩል የአየር ንብረት መዛባት ታክሎበት የሐይቁ ውሃ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ከተገመተው ጊዜ በላይ ለ38 አመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ የካቲት 3 ቀን 1996 ዓ.ም የሐረማያ ሐይቅ ጨርሶ ውሃ የመስጠት አቅሙ እብቅቷል፡፡

በዚህ ምክኒያት የሐረር መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ስራ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ በ1996 ዓ.ም የተፈጠረውን ከፍተኛ የውሃ ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ እቅድ የተሰራው የኢፋባቴ ጥልቅ የውሃ ጓድጓድ እስከ 2003 ዓ.ም እና እስከ 2015 በቂም ባይሆንም በተጓዳኝ አገልግሎት እየሰጠ ቆይቷል፡፡ የሀረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 15/1991 ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የሐረማያ ሐይቅ ከመድረቁ በፊት የመፍትሄ ሀሳብ በመፈለግ የሀረርን የውሃ ችግር ለመፍታት ሲያደርግ በነበረው ጥረት የሐረር መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ከሀሰሊሶ እስከ ሐረር 72 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በመቆፈር ሥራ ላይ ለማዋል በተደረገው ጥረት ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ብድር ሥራውን በማስጀመር 7 ዓመት በፈጀ ጊዜ ሥራው ተጠናቆ በ2003 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት ቢጀመርም ከዚህ በፊት የታዩ ችግሮች የአየር ንብረት መዛባት፣ የህዝብ ብዛት መጨመር የባለስልጣን መ/ቤቱን የውሃ አቅርቦት በቂ ሊያደርገው እና ችግሩን ሊፈታው ባለመቻሉ የሐረሪ ክልል መንግስት ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር በመሆን በየጊዜው ተጨማሪ የውሃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ አገልግሎት ላይ ቢውሉም በቂ ሊሆንና በፈረቃ የሚደርሰውን የውሃ አቅርቦት ትርጉም በአለው መንገድ ሊያሻሽለው ባለመቻሉ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከኤረር ቂሌ አካባቢ ተጨማሪ አዲስ የውሃ መገኛ በማጥናት የግንባታ ሥራውን በ2009 ዓ.ም በማጠናቀቅ በአካባቢ ለሚገኙ የገጠር ማህበረሰቦች እና በከፊል ለሐረር ከተማ ነዋሪዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡