በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሳደግ ተችሏል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ

ሐረር፤መጋቢት 8/2017(ሐክመኮ):-በሐረሪ ክልል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሳደግ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በሐረሪ ክልል ገጠር ወረዳ የተገነቡ ስድስት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። የውሃ ፕሮጀክቱን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ናቸው። ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቶቹን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት በክልሉ በከተማ እና ገጠር የውሃ አቅርቦት ጨምሯል።
በተለይ በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍተ የተደረጉት ፕሮጀክቶች በገጠሩ ክፍል ቀድሞ ይስተዋል የነበረውን የውሃ ተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የሚየስችል ነው። ፕሮጀክቶቹ አርሶ አደሩ ውሃ በአቅራቢያው እንዲያገኝ በማስቻል በውሃ ፍለጋ ያባክኑት የነበረውን ግዜ እና ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት የሚያስቀር መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል። ለፕሮጀክቱ ዘላቂነት የአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊውን እንክብካቤ እና ጥበቃ ሊያድግለት እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል። በሌላ በኩል በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች በተለይ የኮሪደር ልማቱ ማህበረሰቡ ዘንድ መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም በክልሉ በተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት በማጠናቀቅ በዘርፉ የተመዘገበውን ውጤት በጤና፤ትምህርት እና የመልካም አስተዳደር ዘርፍ በመድገም ለህዝብ የገባነውን ቃል የምናድስበት ይሆናል ብለዋል። የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን በበኩለቸው በክልሉ ገጠር ወረዳ በ120 ሚሊዮን ብር በጀት እየተገነቡ ካሉ 14 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅተዋል።
በክልሉ ኤረር እና ሶፊ ወረዳዎች የተገነቡት የውሃ ፕሮጀክቶች የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር፣ የውሃ መቅጃ ቦኖዎች፣ የኤሌክትሪክና የሶላር ሃይል አቅርቦትና ሌሎች ግንባታዎች የተከናወኑላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል። የውሃ ቦኖዎቹን ከዋናው ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የሚያገናኝ የቧንቧ መስመር ዝርጋታም መከናወኑን አቶ ዲኒ ተናግረዋል። በውሃ ፕሮጀክቶቹ የክልሉን የገጠር የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 66 በመቶ ማድረስ ተችሏልም ነው ያሉት።
በተያያዘ ዜና ለክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በ120 ሚሊዮን ብር ለሚገነባው ባለ አምስት ወለል ሕንፃ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኝ ማሳ የተመለከቱ ሲሆን በገጠር ወረዳዎቹ የአስቤዛ ድጋፍም አድርገዋል። በሥነስርዓቱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር፣ የክልሉ መስተዳድር ካቢኔ አባላትና በየደረጃው ያሉ አመራር አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
